አዲስ አበባ ሰኔ 12/2005 አፍሪካን ከበለጸጉ አገሮች ተርታ ለማሰለፍ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ሥር ነቀል የፖሊሲ ለውጥ ማምጣት እንደሚያስፈልግ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሩ አሳሰቡ፡፡ የአህጉሪቱን ዳያሰፖራ የገንዘብ ሃብት ለልማት ምንጭነት ለመጠቀም የፖሊሲ ማነቆዎችን ማላላት ያስፈልጋል አሉ፡፡ ሚኒስትሩ አቶ ሶፊያን አህመድ ዛሬ የአፍሪካ ወጪና ገቢ ንግድ ባንክ 20ኛ የምስረታ በዓል በአዲስ አበባ ሲከበር እንዳስገነዘቡት አህጉሪቱን ካለችበት ደረጃ ለማውጣት ኢኮኖሚያዊ ትራንስፎርሜሽን ትኩረት ሊቸረው ይገባል፡፡ በዚህም የአህጉሪቱን የምርታማነት አቅም ማሳደግ እንደሚገባና አገሮቹ በአብዛኛው ከሚገኙበት የግብርናው ዘርፍ ወደ ኢንዱስትሪው በመሸጋገር እድገታቸውን ማፋጠን እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ ለዜጎቻቸው ምቹ የሥራ ዕድል በመፍጠር ከድህነት አረንቋ ፈጥኖ በመውጣት መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታም እንደሚያስልፋቸው ገልጸዋል፡፡ የአፍሪካ ኢኮኖሚ አሁንም በተፈጥሮ ሀብት ላይ ጥገኛ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፣ በዚህም ሳቢያ በጥሬ ዕቃዎች ላይ ያመዘነው የአህጉሪቱ የወጪ ንግድ ለኢንዱስትሪ ዕድገቱ ደካማነት አመላካች እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ በአህጉሪቱ እርስ በርሱ የሚመጋገብና የተቆራኘ የኢንዱስትሪ ልማት ማምጣት ዋነኛ አማራጭ መሆኑን ገልጸው በዚህ ረገድ አህጉራዊው የወጪና ገቢ ንግድ/አፍሪኤግዚም /ባንክ የተቋቋመበትን ዋነኛ ዓላማም ማጠናከር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡ በባዕድ አገሮች የሚኖሩ ዜጎች ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ብቻ 60 ቢሊዮን ዶላር ወደ የአገሮቻቸው መላካቸውን የዓለም ባንክ መረጃን የጠቀሱት አቶ ሶፊያን፣ ከዚህ ውስጥ 28 ቢሊዮን ዶላር የአፍሪካውያን ድርሻ እንደሆንም ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከዳያስፖራ ዜጎች የገንዘብ ተጠቃሚ አምስት ዋነኛ አገሮች አንዷ መሆኗን አመልክተው፣ በውጭ የሚኖሩ አፍሪካውያን ለማህበረ- ኢኮኖሚ ልማት ያላቸው አስተዋዕኦ ክፍተኛ በመሆኑ ትኩረት እንደሚቸራቸው ተናግረዋል፡፡ የአፍሪካ ዳያስፖራ በየዓመቱ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ አህጉሪቱ ከውጭ ብድርና ዕርዳታ ጋር እንደሚመጣጠን ገልጸዋል። ይህንን በውጭ ባንኮች የተከማቸ የገንዘብ ፈንድ ወደ አህጉሪቱ ለመሳብ አገሮች የአስተማማኝ የፋይናንስ ፖሊሲና ፕሮግራም መቅረጽ እንዳለባቸውም ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል፡፡ የአፍሪ ኤግዚም ባንክ ፕሬዚዳት ሚስተር ዣን ሉዊስ ለጋዜጠኞች እንደገለጹት ባንኩ ለኢትዮጵያና ሌሎች የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ባንኮችና የልማት ፕሮጀክቶች የገንዘብ ድጋፍና ብድር እየሰጠ ነው ፡፡ በኢትዮጵያ 20ኛ የምስረታ በዓሉን ሲያከብር ንግድና ኢንቨስትመንትን ወደ አገሪቱ ለመሳብ ጭምር በማለም መሆኑንም ተናግረዋል። በኢትዮጵያ የኃይል ፍላጎት ፕሮጀክቶች ውስጥም ገንዘቡን ኢንቨስት ማድረጉንም ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡ ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው በዓል ላይ ኤግዚቢሽንና የባህል ትዕይንት ጨምሮ የተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚቀርቡም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል፡፡


አዲስ አበባ ሰኔ 12/2005 ኢትዮጵያ የታላቁ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ከግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ላለ...
አዲስ አበባ ሰኔ 12/2005 በአማራ ክልል በሰሜን ሸዋ ዞን የትምህርት ልማት ሠራዊት በመገንባት የትምህርት ተ...
አዲስ አበባ ሰኔ 12/2005 ኢትዮጵያ ከፍተኛ እምቅ የእጣንና ሙጫ ሀብት ቢኖራትም በግንዛቤ እጥረት የተነሳ በ...